እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ። መዝ 119፡107
የሚታደስ ነገር ሁሉ ችግር ያለበት ነገር ግን ደግሞ የተሻለ ለመሆን ተስፋ ያለው ነው። የሰው ልጅን ብንወስድ ካሉበት እጅግ በርካታ ችግሮች ቀዳሚውና ዋንኛው ኃጢአት ነው። ኃጢአት ከካንሠር የላቀ እጅግ ገዳይና ማንንም ሰው ሰለባ ማድረግ የሚችል ኃያል ነው። ሞትን ያስከትላል፤ ይህም ደግሞ ከተሳካልን በዚህች ምድር የምንኖረውን የ60 እና የ70 ዓመት ዕድሜ ሳይሆን ኃጢአት የዘላለም ሞትን ያስከትላል፤ ሞት የሚባል ደመወዝ አለው፤ ለዘላለም ያጠፋል። መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ይላል፤ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና” (ሮሜ 6፡23)።
ስለዚህ ሁላችን የዚህ ቀሳፊ በሽታ ተጠቂዎች በመሆናችን መታደስና በኃጢአት ላይ ድል መጎናጸፍ ያስፈልገናል፤ ችግር ውስጥ ነው ያለነው። ለዚህም ነው “እጅግ ተቸግሬአለሁ” የሚለው ዳዊት፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ”። “መልሰህ ሕያው አድርገኝ” ማለት “አድሰኝ”፣ “ወደነበርኩበት መልሰኝ”፣ “መልሰህ ወይም እንደገና ሕይወት ዝራብኝ” ማለቱ ነው።
ግን የምንነቃው፤ የምንታደሰው በምንድን ነው? ከእኛ ውጪ የሆነ ኃይል ሊያድሰን ይገባል እንጂ በራሳችን አንችልም። የተኛ ሰው እንኳን የሚያነቃው አንዳች ኃይል ያስፈልገዋል። እኛም መንቃት እንዳለብን እስከምንዘነጋ ድረስ ጭልጥ ያለ የኃጢአት ዕንቅልፍ ውስጥ ስላለን ሊያነቃንና መንፈሳችንን ሊያድስ የሚችለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። መንቃት ብቻ ሳይሆን “ከማይጠፋው ዘር” ሆኖ ዳግመኛ መወለድ፣ መለወጥ ወይም የመንፈስ መታደስ ማግኘት የምንችለው በዚሁ “በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት ነው” (1ጴጥ.1፡23)።
አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሠርተው ከኤድን ገነት ከተባረሩ በኋላ እግዚአብሔር የሰጣቸው ታላቅ ነገር ቢኖር የተስፋ ቃሉን ነበር። እንዲህ አላቸው፤ “በአንተ (በእባብ በተመሰለው ሰይጣን) እና በሴቲቱ (በሔዋን) መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ (የሴቲቱ ዘር ክርስቶስ) ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” (ዘፍ. 3፡15)። በሴቲቱ ሔዋን ስም ቢነገርም ተስፋው ግን ለመላው የሰው ዘር ነበር። ይህ ቃል ነበር የመጀመሪዎቹን ወላጆቻችንን በተስፋ እንዲዘልቁ ያነቃቃቸው። በመጀመሪያ በወለዷቸው ልጆች ቃየንና አቤል ዕውን ይሆናል ብለው ያሰቡት ታላቅ ተስፋ ቃየን ወንድሙን አቤል በመግደል ቢጨልምም በቀጣይ ግን ሌላ ልጅ በወለዱ ጊዜ ሔዋን “ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው” (ዘፍ. 4፡25)። የቃሉ ተስፋ እንደገና ሕያው አደረጋቸው፤ መንፈሳቸውን አደሰላቸው፤ አነቃቸው።
ይህ የእግዚአብሔር ቃል በዘመናትም ሁሉ እንዲሁ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሲያነቃ፣ ሲበረታታ፣ መንፈሱን ሲያድስ ቆይቷል። ኖህ በጥፋት ውሃ ዘመን ለ120 ዓመታት በተስፋ እንዲሰብክ ያደረገው ይህ ቃል ነው። አብርሃምን ከወላጆቹ አገር ወጥቶ ወደማያውቀው ምድር ሄዶ ለመኖር ያደፋፈረውና ያበረታው እግዚአብሔር የገባለት ቃል ነው። እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር ለበርካታ ዓመታት ባርነት ሲማቅቁ ከቆዩ በኋላ ወደተስፋዪቱ ምድር እንዲገቡ ያደረጋቸው ይህ ቃል ነው። የይሁዳ ቤት በአመጻቸው ምክንያት በስደት ወደ ባቢሎን ከሄዱ ከ70 ዓመታት በኋላ ተመልሰው ወደ ምድራቸው እንዲገቡ ያደረጋቸው ነፍስን የሚመልሰው የእግዚአብሔር ቃል ነበር። ከምርኮም በኋላ የመሲሑን መምጣት ያበሰረላቸው፤ መሲሑም ጌታችንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ከመጣ በኋላ በሽተኞችን ይፈውስ፣ ለምጻሞችን እንደ ቀድሟቸው ይመልስ፣ ያድን፣ ያነጻ፣ ሙታንን ሳይቀር ያስነሳ የነበረው በዚሁ ሕያው ማድረግ በሚችለው ቃሉ ነበር።
የእግዚአብሔርን ቃል በመቃወም የአባቶችን ወግ በማስፈን ቤተክርስቲያን ወደ ጨለማ እንድትገባ በተደረገበትና የእግዚአብሔር ቃል በመጥፋቱ በተለምዶ “የጨለማው ዘመን” በሚባለው ወቅት ምድር ከነበረችበት የሞራል መላሸቅ እንደገና እንድታንሰራራ፣ ሕይወት እንደገና እንዲነቃቃ፣ አዳዲስ ነገሮች እንዲፈለሰፉ፣ ኪነጥበብ እንዲዳብር፣ ወዘተ ያደረገው እንደገና መሥራት የሚችለው የእግዚአብሔር ቃል ነበር።
“እጅግ ተቸግሬአለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ” መዝ. 119፡107።
ያለንበት ዘመን የሞራል መላሸቅ ብቻ ሳይሆን እንጥፍጣፊ ሞራል (ግብረገብነት) የቀረ እስከማይመስል ድረስ የወረድንበት ነው። በአገራችን ብቻ የሚሆነውን ማየት ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። የፖለቲካውን ጉዳይ ትተን በቤተእምነቶች አካባቢ ያለውንም ብናይ ውድቀቱ ዘግናኝ ሆኖ እናገኘዋለን። እምነታቸውን በሚታይ መልኩ ባደባባይ የሚመሰክሩ ሰዎች ሌላውን በዘር፣ በጎሣ፣ በወገን ተቧድነው ሲያጠቁ፣ ሲበድሉ፣ ማየት ዕለታዊ ክስተት ሆኗል። የሃይማኖት ሰው እንዴት ሆኖ ነው ዘረኛ የሚሆነው?
በሌሎች ዘንድ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ሲነገር ከመስማት ይልቅ የሰዎች ዲሰኩርና የ“ተገለጠለኝ”፣ የ“ሠይጣንን ወጋሁት” ንግግሮች የእምነት ቦታዎችን ሞልተዋል፤ ምዕመኑም ፍጹም መለወጥ የሚችለውን የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት ይልቅ በስሜት ፈረስ እየተነዳ በምድረበዳ ውሃ አጥቶ እንደሚቅበዘበዝ አሸዋ እየጠጣ በከንቱ ይባዝናል። ሃይማኖት ወደ ሰማይ የሚያደርስ ብቻ ሳይሆን በምድርም መልካም ዜጋ፣ ለሰዎች አሳቢ፣ ማድረጉ ቀርቶ መበልጸጊያ፤ መከበሪያ፣ ዝናን ማትረፊያ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በ“ሼር” እና “ላይክ” መደነቂያ ከሆነ ሰነባብቷል።
በኑሮ አዙሪት ውስጥ የሚንገላታው ሕዝብ ወደቤተ እምነት ሄዶ ማቆሚያ በሌለው መረን የለቀቀ የፈውስና የዝማሬ አዙሪት ውስጥ በመግባት ባዶውን መጥቶ ባዶውን ይመለሳል። ቃሉ ይሰበካል በሚባልባቸው ቦታዎችም ቃሉን ይዘው የሚቀርቡት ሰባኪዎች በቅጡ ተዘጋጅተው የሰውን ልብ በሚያቀልጥ፤ ኃጢአትን በሚወቅስ፤ የሰማይን መንገድ በሚያሳይ ዝግጅት ሳይሆን ያላጠኑትን፤ ያልተዘጋጁበትን የተለመደውን እጅግ አሰልቺ ቃል በመናገር ሕዝብ ከእግዚአብሔር ቃል ድንቅና ተዓምራት እንዳያይ፤ ልቡም በቃሉ ትኩሳት እንዳይቀልጥ አድርገውታል። “ዕንቅልፋም ሰባኪዎች ለዕንቅልፋም ምዕመናን” መስበካቸውን ቀጥለዋል።
ጌታችንና መድኃኒታችን ሞትን ድል አድርጎ ከመቃብር ከተነሳ በኋላ ይህንን ታላቅ እውነት ያልተረዱ ሁለት ደቀመዛሙርት ጌታቸው በመሞቱ ምክንያት አዝነውና ጠውልገው “ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው” እየተነጋገሩ ኤማሁስ ወደምትባል መንደር እየተጓዙ ነበር፤ “ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር” (ሉቃስ 24፡15)። መድኃኒዓለምም በነቢያት የተነገረውን ቃሉን አለማስተዋላቸውን ከወቀሰ በኋላ “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው” (ሉቃስ 24፡27)። በመጨረሻም እንጀራ አንስቶ ባርኮ በሰጣቸው ጊዜ ዓይናቸው ተከፍቶ አወቁት፤ እርሱ ግን ተሰወረባቸው፤ “እርስ በርሳቸውም፦ በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ” (ሉቃስ 24፡32)። አዳኛችን ለእነዚህ ሰዎች ያደረገው ነገር ቢኖር ቃሉን ነው እንዲያስታውሱ ያደረጋቸው። ይህም ሐዘናቸውን አስረሳቸው፣ ልባቸውን አቀለጠው፣ፈወሳቸው፣ አደሳቸው።
የእግዚአብሔር ቃል እሣት ነው የኃጢአትን ቆሻሻ ያቃጥላል፣ ያቀልጣል፤ መዶሻ ነው ራስወዳድነትን፣ እኔነትን፣ ዕብሪትን ይሰባብራል። “በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር” (ኤር. 23፡29)። የአምላካችን ቃል ሰይፍ ነው፤ ትምክህትን ፣ማን አለብኝነትን፣ ወገንተኝነትን፣ ዘረኝነት፣ ማንኛውንም የህይወት ርኩሰት ይቆራርጣል፣ ይበጣጥሳል። ድብቅ ምኞትን፣ አንድም ሰው የማያውቀውን፣ ከሁሉ የደበቅነውን በውስጥ ሃሳብ ብቻ የያዝነውን ይመረምራል፤ ገሃድ ያወጣል፤ እርግፍ አድርገህ ተወው ይላል። “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል” (ዕብ. 4፡12)።
ስለዚህ እንደዚህ ሊለውጥና ማንነታችንን ሊቀይር ወደሚችለው የእግዚአብሔር ቃል እንመለስ። በጸሎትና በትጋት ካጠናነው ከሚያስተምሩን ሁሉ ይልቅ ልናስተውለው እንችላለን (መዝ. 119፡99)። ቃሉ “…ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ” ይጣፍጣል (መዝ. 119፡103)። በምንኖርበት ጨለማ ዓለም መንገዱ ሲጠፋብን፤ አቅጣጫ ስንስት ለእግራችን መብራት፤ ለመንገዳችን ብርሃን ነው (መዝ 119፡ 105)። ታዲያ ይህንን ኃያልና መንፈስን የሚድስ፤ ማንነትን የሚቀይር ቃል እንዴት እናጥናው?
የእግዚአብሔር ቃል በምድር ውስጥ እንደ ተደበቀ ታላቅ ሃብት ነው፤ በትጋት ልንመረምረው ያስፈልጋል። በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን በሰጠው ምሳሌ እንደተናገረው ይህንን ሃብት ያገኘው ሰው መልሶ ሸሸገው፤ “ከመደሰቱም የተነሣ ሄዶ፤ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያንን የዕርሻ ቦታ ገዛ” (ማቲ. 13፡44)። ሰው እንጀራ በመመገብ ብቻ ሳይሆን የሚኖረው የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናትም ጭምር ስለሆነ ከዚህ የሚከተለውን መመሪያ በመከተል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዛሬ መጀመር ይቻላል፤
- ጊዜና ቦታ መወሰን፤ ከእግዚአብሔር ጋር በምንም ቢሆን የማይቋረጥ የቀጠሮ ሰዓት መያዝ፤ የሚመችና ፀጥ ያለ በቀላሉ የማይረበሹበትን ቦታ መምረጥ፤ ቦታውም እንደጊዜው ቋሚ ይሁን፤ በቀደምት ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ በሚከለከልበትና ቅጂውም በጥቂት ሰዎች ዘንድ በሚገኝበት ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ዘንድ በመሄድ ተነብቦላቸው ሲመጡ “መጽሐፍ ቅዱስ አጥንተን መጣን” ሳይሆን እግዚአብሔር ሲናገር ሰምተን መጣን ነበር የሚሉት፤
- ዕቅድ ማውጣት፤ የሚጠናውን መወሰን፤ ርዕስ (ማለትም ስለ ዓለም ፍጻሜ፣ ስለ መዳን፣ ስለ ሙታን ሁኔታ፣ ስለ ምፅዓት፣ ወዘተ) በመምረጥ ማጥናት፤ ወይም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (ለምሳሌ የዮሐንስ ወንጌል) በመምረጥ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ጥናት ማድረግ፤ ወይም ግለታሪክ (ለምሳሌ የአብርሃምን፣ ወይም የሙሴን ወዘተ) በመምረጥ ማጥናት፤
- የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ፤ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ትርጉሞች ስላሉ የተሻለውንና ለመረዳት የሚቀለውን መምረጥ፤
- መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ይተረጉማል፤ ዘመናዊዎቹም ሆነ የቀድሞዎቹም ዕትሞች በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ማጣቀሻ ጥቅሶች አሏቸው፤ እነዚያን በመከታተልና በማንበብ የበለጠ ሃሳቡን ከነዐውዱ መረዳት፤
- አብሮ የሚያጠና ወዳጅ መምረጥ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እየተወያዩና ሃሳቦችን እያፈለቁ ሲያጠኑት የበለጠ ትርጉም ስለሚሰጥ አብሮ የሚያጠና ወዳጅ ከተገኘ በእጅጉ ይረዳል፤
- የተማሩትን በተግባር በሕይወት መተርጎም፤ “በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሚባሉት ለሕጉ የሚታዘዙ እንጂ፣ ሕጉን የሚሰሙ አይደሉም” (ሮሜ 2፡13)።
- ለመማር በሚፈልግ ትሁት ልብ እና በጸሎት መጀመር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስናጠና አስቀድመን በአእምሯችን ያለ አስተሳሰብን ወይም አመለካከት ወይም እምነት እንዲደግፍልን ጥቅስ በመፈለግ ሳይሆን “እግዚአብሔር ምን አዲስ ነገር ያስተምረኛል?” በሚል ክፍት ልብ መጠናት ያስፈልገዋል፤ መጽሐፉ የተጻፈው በመንፈስ ስለሆነ በጸሎት ከፍቶ ማንበብ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራና እንዲተረጉም ዕድል ይሰጠዋል፤ ስለዚህ ጊዜ መስጠት አያስፈልግም፤ ዛሬውኑ፣ መጀመር ነው!
የእግዚአብሔርን ቃል ለራሳችን ስናጠና እንታደሳለን፤ ይህ ተሃድሶ በጸሎት ወደ መነቃቃት ይወስደናል። ያስተምሩናል ከምንላቸው ሰዎች ሁሉ ይልቅ “አስተዋይ ልብ” ይሰጠናል፤ አምላካችን የሚሰጠንን መመሪያ ስንከተል “ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ” እንሆናለን፤ የሰማነውን፣ ያጠናነውን ቃል በተግባር ስንተረጉም፣ ስንጠብቀው እግሮቻችን “ከክፉ መንገድ ሁሉ” ይከለከላሉ (መዝ. 119፡ 99-101)። ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለትዳራችን፣ ለወገናችን፣ ለአገራችን የምንጠቅም መሆን ከፈለግን ካላጠኑት በስተቀር መጣፈጡን ማወቅ የማይቻለውን የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት እናጥና።
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ
1 thought on “መንፈሴን አድስልኝ”