giziew.org

መጽሐፍ ቅዱስና ታሪኩ (ክፍል ፪)፡ መገለጥ!

መገለጥ ምንድነው? ለምንስ አስፈለገ? አምላክ ራሱን በምን መልኩ ነው የገለጠልን? ወዘተ ሃሳቦች በዚህኛው ትምህርት ይመለሳሉ
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በክፍል አንድ ዝግጅታችን መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው? በሚል ርዕስ በጥንት ዘመን መልዕክት እንዴት ይተላለፍ እንደነበር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስሙን ከየት እንዳገኘ፣ የተጻፈበት ዓላማና ቋንቋ ምን እንደነበር፣ ምን ዓይነት ስርዓተ ነጥብ ተጠቅሞ እንደነበር? መጀመሪያ በምን ላይ እንደተጻፈ? የመሳሰሉ ጥያቄዎች በማንሳት ጠቅለል ባለ መልኩ ለመዳሰስ ሞክረናል። በዚህ ክፍል 2 ጽሑፍ ደግሞ ጠለቅ ወዳለ ትንተና በመግባት ስለ መገለጥ እንማራለን።

ኖርማን ኤል ጊዝለር የተባሉ ምሁር በ“A General Introduction to the Bible” በተባለው መጽሐፋቸው፤ መፅሐፍ ቅዱስ ወደ እኛ ለሚያደርሰው መልዕክት አራት ተያያዥነት ያላቸው ሒደቶች እንዳሉ ይናገራሉ። እነርሱም በመንፈስ አነሳሽነት መልዕክት በማምጣት ወይም በመንፈስ መመራት/በመገለጥ ሒደቶች ሲሆን፤ የእያንዳንዳቸው ትርጉም የሚከተለውን ይመስላል።

በመገለጥና በመንፈስ ምሪት መልዕክት መቀበል ወይም በመንፈስ መመራት ማለት እግዚአብሔር መልዕክቱን ለነቢያት በመንፈስ በመገለጥ እንዲመዘግቡት ያደረገበት ሂደት ሲሆን ቀኖና ማለት ደግሞ እነዚህ በነቢያት የተፃፉትን ጽሑፎች ማንነታቸው ወይም ምንነታቸው ፈትሾና ለይቶ እንደ ቅዱስ ጽሑፍ እውቅና አግኝተው ከያሉበት የተሰባሰቡበት ሂደት ነው። ስርጭት ወይም ማስተላለፍ የምንለው ደግሞ እነዚህ በእጅ የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሌሎች እንዲያነቧቸውና ለትውልድ እንዲተላለፉ በመገልበጥ ወይም ኮፒ በማድረግ ቅጂዎቹን አባዝቶ ማስተላለፍ ሲሆን ትርጉም ማለት ደግሞ እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉበትን የመጀመሪያ ቋንቋ ለማያስተውሉ ሰዎች በቀጥታ በየቋንቋቸው እንዲያነቡና እንዲያስተውሉ ተርጉሞ ማቅረብ ነው።

በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ሰጥተን የምንመለከተው ከላይ ከተዘረዘሩት ሂደቶች ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን መገለጥ (Revelation) የሚባለውን ነው። በአማርኛ መገለጥ ብለን የምንጠራው ጥሬ ቃል ትርጉም የተደበቀን መግለጥ፣ የተሰወረንና ድብቅ ሆኖ ያልተረዳነውን ነገር ማስረዳት ወይም መረዳት ማለት ነው። መገለጥ መለኮት ራሱን ለመግለጥ የሚያደርገው ድርጊት ነው። ይህም ድርጊት ነብዩን ከዚህ በፊት ስለአንድ ነገር ወይም ሁነት ሊያውቀው ወይም ሊረዳው የማይችለውን ነገር እንዲያስተውል የሚያደርግ ነው። በመገለጥ ውስጥ የሚደርሰን መረጃ ስለመለኮት ወይም ስለ ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል። ሮጀር ኩን የተባሉ ምሁር መገለጥ ማለት “ከአምላክ ወደ ነብዩ የመጣው የመልዕክት ይዘት ነው” ይላሉ። ስለዚህ መገለጥ የሚያተኩረው የመልእክቱ ምንጭና ይዘት ላይ ነው።

ኃጢአት ወደዚህች ምድር ከገባ በኋላ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው የፊት ለፊት ግንኙነት ተቋረጠ (ዘፍ. 3፡9-12)፤ በዚህም ምክንያት ሰዎች በቀጥታ ከእግዚአብሔር መልዕክትን መቀበል የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። ስለዚህ ከእግዚአብሔር መልዕክትን ወይም መገለጥን የሚቀበል ሰው ወይም ነቢይ እንዲኖር አስፈለገ። ይህ ነቢይ ብለን የምንጠራው ሰው እንደማንኛችንም ኃጢአተኛ ሰው ቢሆንም እንኳ የእግዚአብሔር መንፈስ ግን መልዕክት ይሰጠዋል፤ መልዕክቱንም ለሰዎች ሲያውጅም ሆነ በጽሑፍ ሲያስተላልፍ ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ አብሮት ይሠራል።

መገለጥ ለምን አስፈለገ?

መገለጥ ያስፈለገበት ቢያንስ ሶስት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው፤ የሰው የመረዳትና መርምሮ የማግኘት ወይም የማወቅ ውስንነት ነው። ይህም ወሰን የሌለውንና ከሰው ማስተዋል በላይ የሆነውን አምላክ ለመረዳትና መንገዱን ለማስተዋል መገለጥን አስፈላጊ ያደርገዋል።

ሁለተኛው፤ እግዚአብሔር የግንኙነት አምላክ ከመሆኑ የተነሳና ራሱንም ለእኛ መግለጥ ስለሚፈለግ ነው።

ሶስተኛው፤ ኃጢዓት በሰውና በአምላክ መካከል ያለውን መራራቅ ስላሰፋውና ሰዎችም ከውድቀት በፊት የነበራቸውን አምላክን የመረዳትና የማስተዋል ችሎታቸው በመጎዳቱ ምክንያት ነው።

ስለዚህ ሰዎች በራሳቸው ጥረት ብቻ አምላክን ለማስተዋል ስለሚቸገሩ አምላክ በመንፈሱ ራሱን እንዲገልጥላቸው ያስፈልጋል ማለት ነው።

መገለጥ

አምላካችን እግዚአብሔር “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና” (ዕብ. 1፡1) ከጥንት ጀምሮ ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት ሲያደርግ የኖረ አምላክ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ለሰው ልጆች መልዕክትን ይገልጣል ወይም ይልካል። ከነዚህ የተለያዩ መንገዶች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፤ በመላዕክት (ዘፍ. 18)፣ በሕልም (ዳን. 7፡1፤ ዘኁ. 12፡6)፣ በራእይ (ኢሳ. 1፡1፤ ሕዝ. 1፡1፤ 8፡3)፣ በተዓምር (ዘጸ. 3፡2፤ መሳ. 6፡37፤ ዮናስ 4፡6)፣ በተፈጥሮ (መዝ. 19፡1)፣ በድምጽ (1 ሳሙ. 3፡4)፣ በኅሊና ድምጽ (ሮሜ 9:1-2፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል የሚሉት አገላለጾች እንደ አስረጅ ሊወሰዱ ይችላሉ፤(ዘጸ. 5፡1፤ ኢሳ. 1፡24)፣ በኡሪም ቱሚም (ዘጸ. 28፡30፤ ዘኁ. 27፡21)፣ ዕጣ በመጣል (ምሳሌ 16፡33) እና የሌሎችን ነቢያት ጽሑፍ ማጥናት (ዳን. 9፡1-2) ናቸው።

ይህን ከአምላክ የሚመጣ መገለጥ የስነመለኮት ምሁራን በሁለት ይከፍሉታል። እነርሱም የወል (ጠቅላላ) መገለጥ (General Revelation) እና ልዩ (የተለየ) መገለጥ (Special Revelation) በመባል ይታወቃሉ።

ጠቅላላ መገለጥ በመባል የሚታወቀው ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም ጊዜና ቦታ ስለ እግዚአብሔር የሚያስረዱን ነገሮች ናቸው። የተለየ መገለጥ ብለን የምንረዳው ደግሞ ለተለዩ ሰዎች፣ በተለየ ጊዜና ቦታ የቀረቡ መልዕክቶች ናቸው። ጠቅላላ/የወል መገለጥ የተባለው በፍጥረት በኩል የተገለጸ ሲሆን ልዩ መገለጥ የተባለው ደግሞ በነቢያቱ በኩል የሚመጣ በጽሑፍ የሚተላለፍ መገለጥ ነው። ዛሬ ይህ ልዩ መገለጥ ወይም የጽሑፍ መልዕክት የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ነው።

ጠቅላላ ወይም የወል መገለጥ

ጠቅላላ ወይም የወል መገለጥ የምንለው እግዚአብሔር በተፈጥሮ፣ በታሪክ ውስጥ እና በሰብዓዊ ይዘቶች ውስጥ ስለራሱ የገለጸልን ነው። በገሃዱ ዓለም ወይም በተፈጥሮ ወይም በፍጥረታት፣ በሰብዓዊ የማመዛዘን ሂደቶችና በደመነፍስ በኩል የምናገኘው መረዳት እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት መንገድ ስለሆነ የወል (ጠቅላላ) መገለጥ በመባል ይታወቃል። ጠቅላላ መገለጥ የተባለበት ምክንያት ለማንኛውም ሰው በአንድ ጊዜ ተደራሽነት ያለው በመሆኑና የሚያስተላልፈውም መልእክት ጠቅለል ያለ ከመሆኑ የተነሳ ነው።

በመጀመሪያ የዚህን ጠቅላላ መገለጥ የምናስተውልበት ቦታ ተፈጥሮ ውስጥ ነው። በተለይ ስለ አምላክ በተፈጥሮ ውስጥ መገለጥን የሚያስረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በመዝሙር 19፣ 1-4፤ በሐዋ. ሥራ 14፡17 ና በሮሜ 1፡ 20-21 ይገኛሉ።

ለምሳሌ ስለ አምላክ መኖር ከሚቀርቡት አስረጂ ነጥቦች መካከል አንዱ የሆነው ፈለካዊ ክርክር (cosmological argument) የሚባለው መከራከሪያ ነጥብ የአምላክን ኅልውና የምንገነዘበው በፍጥረታት ውስጥ በምንመለከተው ውበትና ልዩ ሞገስ ምክንያት ነው ይላል። መጽሐፍ ቅዱስም ለዚህ መከራከሪያ ነጥብ በሮሜ 1፡ 20-21ላይ እንዲህ ይላል።“የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ”።

ተፈጥሮ ላይ በመመርኮዝ የሚቀርበው ሌላኛው መከራከሪያ ነጥብ ደግሞ መነሾ-ፍጻሜ ክርክር (teleological argument) የተባለው ሲሆን ስለ እግዚአብሔር ኅልውና ያስረዳል ብሎ የሚያቀርበው ነጥብ በፍጥረታት ውስጥ የምንመለከተውን የተለያየ ንድፍ ወይም ዲዛይን፣ ሞድ (ሁኔታ) እና ስርዓት አስደናቂነት ከዓላማው ወይም ከመጨረሻው ተነስቶ በማሳየት ነው። እነዚህ ነገሮች ስለ አምላክ መኖርና ፈጣሪነት የሚያስረዱ፤ የሚመሰክሩና የሚናገሩ ናቸው።

ሁለተኛው ጠቅላላ መገለጥን የምናገኝበት ቦታ ደግሞ በታሪክ ውስጥ ሲሆን ይህም እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለውን በቅርበት በመመልከት ልንረዳ የምንችለው ነው (ዳን. 2:24-49)።

በሶስተኛ ደረጃ ጠቅላላ መገለጥን የምንገነዘበው የሰውን ልጅ አካላዊና አእምሮአዊ ችሎታዎችን በመመልከት ሲሆን የሰው ሞራላዊ የሆነ ተፈጥሮአዊ ይዘቱ፣ ክፉንና ደጉን ለማመዛዘንና ለመምረጥ መቻሉ፣ በተጨማሪም ለመንፈሳዊ ጉዳይ ያለው ከፍተኛ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ስለ ፈጣሪ አምላክ የሚገልጠው ነገር ነው (ዘፍ. 1:26፣27)።

እንግዲህ ይህ የወል (ጠቅላላ) መገለጥ ስለ እግዚአብሔር መኖር ብቻ የሚያስረዳ ሳይሆን እንዲያውም ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት፣ የመፍጠር ችሎታ፣ ውበትን መውደድ፣ የጥበቡን ጥልቅነት፣ ሚዛን የጠበቀ መሆንና ድንቅነቱን ያሳያል። በተጨማሪ ጠቅላላ መገለጥ ሰው ሁሉ የተወሰነ ነገር ስለ አምላክ የሚያውቀው እንዲኖረውና ሰዎች ሁሉ የራሳቸው የሃይማኖት ዝንባሌ ወይም አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ አስተዋጽዖ አድርጓል። ታዲያ ይህ የወል መገለጥ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጀርባ መኖሩን ከማስረዳት ውጪ ብዙ የሚሰጠን ተጨማሪ ምሪት ባለመኖሩ ምክንያት የበለጠ ስለ አምላክ በጥልቀት ለመረዳት ልዩ የሆነ መገለጥ አስፈልጎናል።

የተለየ መገለጥ

ከላይ ስለ ልዩ መገለጥ የተሰጠው ትርጉም እንደተጠበቀ ሆኖ ልዩ መገለጥ የምንለው በቀጥታ አምላክ ራሱን ገልጦልን የምንረዳበት ወይም የምናስተውልበት መንገድ ነው። ይህም በራዕይ፣ በህልምና በድምጽ ነቢያት የተቀበሉትን ምሪት በጽሑፍ ለእኛ በማስተላለፋቸው ምክንያት ያገኘነው ነው (መዝ. 19፡7-14፣ ዕብ. 1፡1-3)።

እንግዲህ በልዩ መገለጥ በኩል ካልሆነ በስተቀር ስለ እግዚአብሔር ልንገነዘባቸው የማንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ኅብረት ሊኖረው እንደሚፈልግ ወይም መድኃኒዓለምን በማመን ስለሚገኘው መዳን መረዳት የምንችለው በዚህ ልዩ መገለጥ በኩል ካልሆነ ፍጥረትን በመመልከት ብቻ መረዳት የሚቻል አይደለም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳችን ስለ እግዚአብሔር የሚያስረዳን ልዩ መገለጣችን እና ዋና ወይም ቀዳሚ ምንጫችን ነው። ለዚህ ደግሞ 2ኛ ጢሞ. 3፡16-17፣ 2ኛ ጴጥ. 1፡20-21 ደጋፊ መረጃ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ።

ይህ የተለየ መገለጥ የራሱ የሆኑ ባህሪያት አሉት። ከነዚህ ባህሪያት መካከል አንደኛው የግል ልምምድ ሲሆን እግዚአብሔር ለግለሰብ ወይም ለሕዝብ ራሱን በስሙ ሲያስተዋውቅ ወይም ቃልኪዳን ሲገባ በታየው ልምምድ ላይ የተገለጸ ባህርይ ነው። ሁለተኛው የተለየ መገለጥ ባህርይ ደግሞ ሰብዓዊ ፍጥረት ሊረዳው በሚችልበት ቋንቋና ደረጃ የተገለጠ መሆኑ ነው። በመለኮታዊ ቋንቋ የተገለጠ ቢሆን ኖሮ ሰዎች ሁሉ ሊያስተውሉት ባለመቻላቸው ምክንያት ይቸገሩ እንደነበር ለሁላችንም ግልጽ ነው። በመጨረሻም በዚህ ልዩ መገለጥ ውስጥ ከምንመለከታቸው ባህርያት መካከል የምናስተውለው ነገር ንጽጽራዊ መሆኑን ነው። ከሰብዓዊው ዓለም የተወሰዱ ነገሮችን በማነጻጸር ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን እንዲያስተውሉ ለማድረግ ይሞክራል። ለምሳሌ ስለፍቅር ስንነጋገር የአምላክ ፍቅር ደረጃው እጅግ ከፍ ያለ ቢሆንም እንኳ ከእናትና አባት ፍቅር ጋር በማነጻጸሩ ምክንያት ለእኛ ይህንን ፍቅር ለመረዳት እጅግ ያቀልልናል። (ኢሳ. 49፡15) “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን እልረሳሽም”።

በተጨማሪ ይህ የተለየ መገለጥ ወደ ሰዎች ልጆች የደረሰበት ሶስት የተለያዩ መንገዶች (ሞዳሊቲዎች) አሉ። እነርሱም በታሪካዊ ሁነቶች፣ በመለኮታዊ ንግግሮችበአምላክ ሥጋ መልበስ (ምሥጢረ ሥጋዌ) በኩል የተገለጹት ልዩ መገለጦች ናቸው።

ታሪካዊ ሁነቶች በኩል የተገለጸው ይህ ልዩ መገለጥ ለምሳሌ በሚከተሉት የታሪክ ይዘቶች በኩል ተብራርቷል። የአብርሃም እንዴት እንደተጠራ፣ በዮሴፍ ዘመን እግዚአብሔር ሰዎችን እንዴት ከረሃብ እንደታደገ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እንዴት ከባርነት ቀንበር ነጻ እንዳወጣቸው፣ የተስፋይቱን ምድር እንዴት እንዳወረሳቸው፣ ተመልሰው ወደ ምርኮ አገር መወሰዳቸውና ከምርኮ ነጻ ወጥተው ወደ አገራቸው መመለሳቸው፣ የክርስቶስ ኢየሱስ መወለድ፣ መኖር፣ መሞትና ከሞት መነሳት፣ ወደ ሰማይ ማረግ፣ የቤተክርስቲያን በዚህ ምድር መኖርና መስፋፋት፤ ወዘተ እነዚህ ሁሉ በታሪካዊ ይዘቶች ውስጥ ልዩ መገለጥ የተላለፈበት አንደኛው መንገድ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ መለኮታዊ ንግግር የምንለው ነው። ለምሳሌ “የእግዚአብሔር ቃል እንደዚህ ሲል ወደ እኔ መጣ”፣ ወይም “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በሚሉት አገላለጾች የተዘረዘሩ ሃሳቦች በዚህ ሥር የሚካተቱ ናቸው (ኤር. 1፡18፣ ሕዝ. 12፡ 1፣8፣17፣21፣26፤ሆሴዕ 1፡1 ኢዩኤል 1፡1 አሞጽ 3፡1 ይመልከቱ)። አምላክ በዚህ መለኮታዊ ንግግሩ ስለራሱ ይናገራል፤ ዕቅዱን ያሳውቀናል፤ ፈቃዱን ይነግረናል። ይህ ልዩ መገለጥም በሚሰማ ድምጽ፣ በጸጥታ ውስጥ፣ በህልም፣ በራእይና በመሳሰሉት መንገዶች መልዕክቱ ለነቢያት ደርሷል።

በመጨረሻም ይህ ልዩ መገለጥ የመጣው በዚህ ምድር ላይ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ (ምሥጢረ ሥጋዌ) አማካኝነት ነው። ይህ ደማቁና ከፍ ያለው መገለጥ ነበር። ኢየሱስ በተናገረበት ጊዜ አምላክ ራሱ ነበር የተናገረው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ከፍተኛውና ሙሉው መገለጥ ነበር። ዕብራውያን 1፡1-2 እንደዚህ ይለናል፤ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” (በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ ዮሐ. 14፡9፤ 1ኛ ዮሐ. 1-2)።

እንግዲህ መገለጥ የብርሃን መምጣትን የሚያስታውሰን ነው። ብርሃን ደግሞ በባሕርይው በጨለማ ውስጥ የተደበቀን ይገልጣል፣ ጨለማን ያባርራል፣ ብርሃን ሲሰፍን ጨለማ ቦታ አይኖረውም። በብርሃን ኃይል ማየት እንችላለን፤ መጽሐፍ ቅዱሳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ብርሃናችንና ታላቁ መገለጣችን ነው (መዝሙር 119፡105)፤ ስለዚህ ለዚህ መገለጥ ክብር በመስጠት እናንብበው ምክሩንም በመከተል እንታዘዝ። “እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ችላ ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን?” (ዕብ 2፡3)

ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ


ዋቢ መጻሕፍት

Coon, W. Roger. “Inspiration/Revelation: What It Is and How It Works. Part I: The Prophetic Gift in Operation.” The Journal of Adventist Education.Vol 44, No. I October-November, 1981.

Geisler, Norman L. and William E. Nix, A General Introduction to the Bible Revised and Expanded. Chicago, Ill.: Moody Press, 1968

Reid, George W. ed. Understanding Scripture: An Adventist Approach. Biblical Research Institute, Silver Spring: Review Herald, 2005.

Song, Ho Kyung. Revelation, Inspiration, and Prophetic Guidance. Adventist International Institute of Advanced Studies, n.d.

Wegner, Paul D. The Journey from Texts to Translations. Grand Rapids, Michigan Baker Academic 2004.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *