giziew.org

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል ?

ስድሳ ስድስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሦስት አህጉራት፤ በሦስት ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፤ ጸሐፊዎቹ ወደ 40 የሚጠጉ ሲሆን ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጥያቄ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለራሱ ምን ይላል?

መልስ፤ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉት እንጂ ሰዎች በገዛ ፈቃዳቸው የጻፉት አይደለም፤ በመሆኑም ይህንን መጽሐፍ ማንም ሊሽረው አይችልም። “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው” (2ጢሞ. 3፡16)፤ “ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም (2ጴጥ. 1፡21)፤ “መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና” (ዮሐ. 10፡35)።

ጥያቄ፤ ካለንበት ዘመን አኳያ በዚህ ዕድሜ ጠገብ መጽሐፍ በእርግጥ መታመን ይቻላል?

መልስ፤ ያለ ጥርጥር መታመን ይቻላል። እንዲያውም የተቃጣበትን ጥቃቶች በሙሉ ተቋቁሞ እስከዚህ ዘመን ድረስ መቆየት መቻሉ አንዱ እንድንታመንበት የሚያደርግ ነገር ነው። ከዚህ ባለፈ ግን በ1ጴጥ. 1፡25 ላይ “የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። ይህ በ1,500 ዓመታት የጊዜ ገደብ ውስጥ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል በትንቢት የተናገረውን ቃል ሁሉ በመፈጸም የታሪክ ማረጋገጫ ያገኘ መሆኑ ሌላው የመታመኛ ማስረጃው ነው።

ጥያቄ፤ አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ በስህተት የተሞላ ነው፤ እንዴት በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ ሊባል ይችላል? ይላሉ።

መልስ፤ መጽሐፍ ቅዱስን አስደናቂ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በውስጡ የተካተተው የመልዕክት አንድነት ነው። ስድሳ ስድስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሦስት አህጉራት፤ በሦስት ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፤ ጸሐፊዎቹ ወደ 40 የሚጠጉ ሲሆን ከእነዚህም ነገሥታት፣ እረኞች፣ ጠበቆች፣ ሳይንቲስቶች፣ የጦር ጄኔራሎች፣ ዐሣ አጥማጆች፣ ካህናትንና ሐኪምን ያካተተ ነው፤ የተጻፈው በ1,500 ዓመታት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሲሆን አብዛኛዎቹ ጸሐፊዎቹ በሕይወት ዘመናቸው ተገናኝተው የማያውቁና የማይተዋወቁ ነበሩ። ይህ ሐቅ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት የሚያረጋግጥ ሲሆን የአምላክ ሃሳብ በሥጋ ለባሽ ሰው ሲገለጽ አንዳንድ ከትርጉምና ከአጻጻፍ ግድፈት የተነሳ ጥቃቅን የሚባሉ ስህተቶች ቢገኙበትም የመልዕክቱ አንድነትና ወጥነት የእውነተኛነቱ ማረጋገጫ ነው። 

ጥያቄ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት ታሪካዊ ክስተቶች ትክክለኛ ናቸው?

መልስ፤ አንዳንዶቹን በቂ የታሪክ ማስረጃ ባለመገኘቱ ለማረጋገጥ ባይቻልም በየጊዜው በተደጋጋሚ የተገኙ ማስረጃዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል፤

(1) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሒታውያን የሚባሉ ሰዎች (ዘዳ. 7፡1)፤ ነነዌ (ዮናስ 1፡1፣2) እና ሰዶም (ዘፍ. 19፡1) የሚባሉ ከተሞች በመጠቀሳቸው ተጠራጣሪዎች ለበርካታ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት ነው፣ እንደዚህ የሚባሉ ከተሞች የሉም ሲሉ ነበር። በዘመናዊ የሥነ-ቅርስ (አርኪዎሎጂ) ምርምር ሰዎቹም ከተሞቹም የነበሩ ለመሆናቸው ማስረጃዎች ተገኝተዋል።

(2) በዳንኤል 5፡1 ላይ የተጠቀሰው የባቢሎኑ ንጉሥ ብልጣሶር እና ኢሳይያስ 20፡1 ላይ የተጠቀሰው የአሦር ንጉሥ ሳርጎን በታሪክ የሌሉ ነገሥታት ናቸው በማለት ተቺዎች ሲናገሩ የነበረ ቢሆንም በርግጥ በሥልጣን ላይ የነበሩ ነገሥታት እንደነበሩ ታሪክ አረጋገጧል።

(3) “ከዚያም ሙሴ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ጻፈ” ብሎ በዘጸ. 24፡4 ላይ መጻፉ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም በሙሴ ዘመን ጽሁፍ አልነበረም በማለት እንዲሁም በዘጸአት 14፡25 ላይ “የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው” ብሎ የጻፈው ስህተት ነው በዚያን ዘመን እንዲህ ዓይነት ክብ ተሸከርካሪ ሊኖር አይችልም የሚሉ ነበሩ፤ ግን የቃሉ እውነተኛነት በዚህ ዘመን እንደገና ተረጋግጧል።

(4) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱት 39 የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት በተመለከተ ይህንን ያህል ነገሥታት አልነበሩም በሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ነበሩ። በዘመናችን በተደረጉ የሥነ-ቅርስ ምርምሮች እነዚህ ነገሥታት ስለመኖራቸው በቂ ማስረጃዎች ተገኝተዋል።

በዝግጅት ክፍሉ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *