giziew.org

ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብኝ

ኃጢአታችን ከተሰማን፣ ኅሊናችን ከወቀሰን፣ ቃሉን ለማጥናትና ለመጸለይ ግድ የሌለን መሆኑ ከተሰማን፣ የምንናገረው ሌሎችን እንደሚጎዳ እየተሰማን ከሆነ፣ ቂምና ጥላቻ እንዳለብን ልባችን የሚነግረን ከሆነ፣ ወዘተ መንፈስ ቅዱስ አልተወሰደብንም ማለት ነው።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

“ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” መዝ. 51፡11

ይህ መዝሙር በኃጢዓቱ አምላክን እንዳስቀየመ የተሰማው ሰው የጸለየው ጸሎት ነው። በርግጥም እግዚአብሔር “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና” በማለት በዘፍጥረት 6፡3 ላይ አምላክ ሰውን በመፍጠሩ በተጸጸተ ጊዜ የተናገረው በተመሳሳይ መልኩ እንዳይደርስበት የፈለገ ሰው ጸሎት ይመስላል። ይህ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም” የሚለው ጥቅስ ከጥፋት ውሃ በፊት አምላክ የሰው ኃጢያትና ክፋት እየጨመረ በቀጠለበት ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ሁልጊዜ ሰውን እየለመነ እንደማይቀጥልና በቃ የሚባልበት ወቅት እንዳለ የሚያስረዳ ነው። ዳዊትም በሠራው ኃጢያት ምክንያት አምላክ መንፈሱን ከሱ ላይ ይወስድብኛል ብሎ በመስጋት የጸለየው የተማጽንዖ ጸሎት ነው።

ዳዊት ንጹህ ልብ አልነበረውም

የመዝሙረ ዳዊት 51፡11ን ሃሳብ ለማግኘት፣ ፍንጭ የሚሰጠንና መንደረደሪያ የሚሆን ሃሳብ የምናገኘው ከፍ ብሎ በተጻፈው ጸሎት ላይ ነው። ይህም “አቤቱ ንፁህ ልብን ፍጠርልኝ። የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” ይላል። ይህ ጸሎት እግዚአብሔርን ከማወቁ በፊት ስለነበረው ዳዊት አልነበረም የሚናገረው። “የእግዚአብሔር ሰው” የተባለው ዳዊት የጸለየው ጸሎት ነው። እርሱ ያልነጻ ልብ እንደነበረው ታውቆታል። በፈጸመው ኃጢአት ልቡም ሆነ ሰውነቱ ሁሉ መቆሸሹን ተረድቶ በሂሶጵ እንዲረጭና ታጥቦ እንዲነጻ ይለምናል።

ታዲያ ይህ ዳዊት የማያምን የነበረ ሳይሆን፤ እንደልቤ የተባለው ዳዊት ነው። ይህ ዳዊት “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝም የለም” ብሎ የዘመረው ነው። ይህ ዳዊት በእግዚአብሔር ንጉሥ ሆኖ እንዲገዛ የተመረጠው ነው። እግዚአብሔርን ያውቃል፤ ልቡ ግን ያልነጻ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪ ነው ነገር ግን ንጹህ ልብ አልነበረውም። የአምልኮ ዝማሬዎችን የጻፈ ነበር፤ ነገር ግን ንጹህ ልብ አልነበረውም። ስለዚህ ነበር ዳዊት ስጋቱንና ፍራቻውን እንዲህ በማለት የገለጸው፤ “ከፊትህ አትጣለኝ መንፈስ ቅዱስህንም አትውሰድብኝ”።

አንድ ሰው ራሱን ሊዋሽ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ግን ቀስ በቀስ ልቡ እውነታውን ይነግረዋል። እኛ ሰዎች በፍጥነትም ይሁን በዝግታ ወይም ቀስ በቀስ ልባችን ሁልጊዜ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ይነግረናል። እንደምናስታውሰው ዳዊት የእስራኤል መሪ እንዲሆን ሲመረጥ ለነብዩ ሳሙኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ የሚል ነበር፤ “እግዚአብሔር ሰው እንደሚያይ አያይም፣ ሰው ፊት ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” (1 ሳሙ. 16፡7)። ይህ በእግዚአብሔር ታይቶ የተወደደው የዳዊት ልብ አሁን ቆሸሸ፤ በደንብ አጥቦ የሚያነጻውን ሂሶጵ ፈለገ።

የዳዊትን ልብ ያቆሸሸው ምንድን ነው?

ዳዊት መዝሙር 51ን የጻፈው ነብዩ ናታን ዳዊትን ከቤርሳቤህ ጋር በፈጸመው ኃጢዓት ምክንያት ከወቀሰው በኋላ ነበር ። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ነገሥታት ወደ ጦር በሚወጡበት ወራት ንጉሡ ዳዊት ሠራዊቱን ወደ ጦር ሜዳ ልኮ እርሱ ከቤተመንግሥቱ ቀርቶ ነበር (ታሪኩ 2ሳሙኤል 11 እና 12 ላይ ይገኛል)። መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት ወደ ኋላ ለምን እንደቀረ ምክንያቱን አይነግረንም። ምናልባት ያለእርሱ መገኘት ሠራዊቱ የጦርነት ተልዕኳቸውን በሚገባ መፈጸም እንደሚችሉ ተማምኖባቸው ሊሆን ይችላል። ወይም መከታተል የሚገባው የአገር ውስጥ ጉዳይ ገጥሞት ይሆናል።

ለማንኛውም ከቤተመንግሥቱ ሠገነት ላይ ሆኖ ሲንጎራደድ አንዲት ቆንጆ ገላዋን ስትተጣጠብ አየና ስለማንነቷ ጠየቀ። ባለትዳር መሆንዋን ቢረዳም እንኳ ወደ ቤቱ ከማስጠራት ወደ ኋላ አላለም። ከእርሷም ጋር አመነዘረ። በዚያን ዘመን ንጉሡ በአገሩ የሚገኙ ያላገቡ ሴቶችን ወስዶ የራሱ ማድረግ ይችል ነበር። ያገባች መሆኗን እያወቀ እርሷን በመውሰድ “አታመንዝር” የሚለውን ሕግ ተላለፈ። በመቀጠልም “አርግዣለሁ” የሚለው የሴትየዋ መልዕክት ንጉሡን ድንብርብሩን አውጥቶ ታላቅ ሥጋት ላይ ጣለው። ኃጢዓቱን ለመሸፈን ዘዴዎችን አቀነባበረ። ቅዱሱ መጽሐፍ “ኃጢአታችሁ ታገኛችኋለች” እንደሚለው የኃጢዓቱን ውጤት ፊት ለፊት መጋፈጥ ግድ ሆነበት። የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅ የተሰወረ ነገር የለምና።

ኃጢዓቱን ለመሸፈን ሊጠቀምበት ካሰባቸው ዘዴዎች መካከል አብራ ያመነዘረችውን ሴት ባል፣ ኦርዮንን ማስገደልና እርሷን ሚስት አድርጎ መውሰድ ነበር። ይህንንም ፈጸመው። “ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ”። ነብዩ ናታንም ወደ ዳዊት መጥቶ ኃጢያቱን ገለጸበት፤ የተፀነሰውም ልጅ እንደሚሞት በእግዚአብሔር ቃል ተናገረ። ጥቂት ቆይቶም ልጁ ታሞ ሞተ።

ዳዊት የፈጸመው ኃጢዓት ወደ ሌላ ኃጢዓት መራው፤ መጀመሪያ አመነዘረ፣ ቀጥሎም ነፍስ አጠፋ። ለቤተሰቡ ሃዘንና ሃፍረትን አመጣ። ለሃገሩም ብጥብጥና የንጹህ ደም መፍሰስ ምክንያት ሆነ። እነዚህ ሁሉ የዳዊትን ልብ ያቆሸሹት ድርጊቶች ነበሩ ። ስለዚህ ነበር ነቢዩ ናታን መጥቶ “ያ ሰው አንተ ነህ” ካለው በኋላ ዳዊት እግዚአብሔርን ንጹህ ልብ እንዲሰጠው የለመነው (2ሳሙ. 12፡7)።

ኃጢዓትን በግልጽ መናዘዝ

የዳዊትን ንስሃ መግባት በደንብ የምንረዳው ሁኔታው በግልጽ ተጽፎ ማንበብ ስለቻልን ነው። በምሳሌ 28፡13 ላይ “ኃጢአቱን የሚሸሽግ አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተዋት ግን ምህረትን ይቀበላል” ይላል። ይቅር የማይባል ኃጢዓት ምልክቱ ሰው ኃጢአትን በመፈጸሙ የማይጸጸት ሲሆንና በደነደነ ልብ በጥፋቱ እየቀጠለና እየገፋ ሲሄድ ነው። በእንደዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ሕይወት ከእግዚአብሔር ተቀባይነትን ያጣል። መንፈስ ቅዱስም ለምኞቱና ለፍላጎቱ ይተወዋል። እንደዚህ ዓይነት የንስሐን ዕድል የሚገፋ ሰው፤ የሰማይን በር ቁልፍ ተቀብሎ ቁልፉን አልፈልግም ብሎ ወደ ባሕር ውስጥ በወረወረ ሰው የሚመሰል ነው። በርግጥ ለአንዳንዶች ኃጢአትን እንደሠሩ ወዲያው ማመን ከባድ ነው። ሌላውን ሰው እንደጎዱ ማመን ያስቸግራል። 1ዮሐ 1፡9 እንደሚገልጽልን ግን “በኃጢአታችን ብንናዘዝ፤ እርሱ የታመነና ጻድቅ ነው፤ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከአመጻም ሁሉ ሊያነጻን” ይችላል። እንግዲህ ኃጢአትን መናዘዝ ማለት እንዴት እንደሆነ ለመረዳት እንዲችሉ መዝሙረ ዳዊት 51ን ደጋግሞ ማንበብ፣ በዚያ ላይ መጸለይ፣ ማጥናት፣ በቃል ማስታወስ ወሳኝነት ያለው ነው።

መንፈስህን አትውሰድብኝ

በመቀጠልም ዳዊት በቁ.11 ላይ “ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብኝ፤ ከፊትህም አትጣለኝ” በማለት ይጸልያል። በርግጥ ይህ ጸሎት በኃጢአት ውስጥ የወደቀ ሰው ሊጸልየው የሚገባ ጸሎት ነው። በንሰሐ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ከትናንሽ ኃጢአቶች ይልቅ እንደዚህ የገዘፉ ኃጢአቶችን ከፈጸሙ በኋላ የበደለኝነት ስሜቱ ጠንካራ ነው። ትናንሽ ኃጢአቶችን ግን ሰውነታችን ይለምዳቸውና ኃጢዓት መሆናቸው እንኳ ሳይሰማን ከእግዚአብሔር ብዙ እንድንርቅ ሊያደርጉን ይችላሉ። በእንግሊዝኛ “አንድ አንበሳ ያደነውን ስልቅጥ አድርጎ በሚጨርስበት ፍጥነት ጥቃቅኗ ትል እንዲሁ አንድን በድን በልታ መጨረስ ትችላለች” የሚል አባባል አለ።

ኃጢአተኛ መሆናችን የሚሰማን ከሆነ፤ እየደጋገመ እግዚአብሔርን የሚበድል ሕይወት ካለን? ማመንዘር ሊሆን ይችላል ወይም ነፍሰ መግደል፣ መሳደብ፣ ውሸት፣ ሐሜት፣ ፍትወት፣ ምኞት፣ ወዘተ ሕግ ተላላፊዎች ነን፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ጸጋ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንደሚኖርና እንደማይወሰድብን መገንዘብ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ጸጋ ሁልጊዜ ከማንኛውም ነጠላ ኃጢአት ወይም የኃጢአት ክምችት የበለጠ ነው (ሮሜ 5፡20-21)። ኃጢአታችን ከተሰማን፣ ኅሊናችን ከወቀሰን፣ ቃሉን ለማጥናትና ለመጸለይ ግድ የሌለን መሆኑ ከተሰማን፣ የምንናገረው ሌሎችን እንደሚጎዳ እየተሰማን ከሆነ፣ ቂምና ጥላቻ እንዳለብን ልባችን የሚነግረን ከሆነ፣ ወዘተ መንፈስ ቅዱስ አልተወሰደብንም ማለት ነው። ስለዚህ እንደ ዳዊት “ከፊትህ አትጣለኝ ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብኝ” ብለን እንጸልይ።

በመዝሙረ ዳዊት 51 የሚገኘውን የዳዊትን ፀሎት ከሉቃስ 15፡ 19 ላይ ከሚገኘው ከአባካኙ ልጅ ፀሎት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። አባካኙ ልጅ ወደ ቤቱ ሲመለስ “አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፣ ወደፊት ልጅህ ልባል አይገባኝም” ብሎ አባቱን ሲለምን፤ ዳዊት ደግሞ “ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብኝ” ብሎ ለመነ። ከቤተሰብህ አባላት መካከል ከመሆን እንዳልሰረዝ ወይም እንዳልወገድ ኃጢያቴን እናዘዛለሁ፣ ለምህረትህ እጮኻለሁ፣ ከእግዚአብሔር ልጆች መካከል እንድገኝ እለምናለሁ አለ። እንደዚህ ዓይነት ጸሎት መፀለይ ካልቻልን ምናልባት የኃጢአታችን ክብደቱ አልታየንም ማለት ነው።

ለመሆኑ ዳዊት ከፊትህ አትጣለኝ፣ ቅዱስ መንፈስህንም አትውሰድብኝ በማለት ሲጸልይ ከዚህ በፊት ከእግዚአብሔር ፊት የተጣሉ የትኞቹን ሰዎችን አስቦ ይሆን?

ከኤደን ገነት የተባረረውን አዳም አስቦ ይሆንን? … ወይስ የገዛ ወንድሙን የገደለውንና ከእግዚአብሐር ፊት ርቆ የተቅበዘበዘውን ቃየንን? … ወይስ የእግዚአብሔርን መንፈስ የቀመሰውን፣ በንዴትና በፍትወት ስሜት የረከሰውን ሳምሶንን?… ወይም ደግሞ ከነቢይነት ወደ ጥንቆላና ምዋርት የወረደውን ንጉሥ ሳዖልን አስቦ ሊሆን ይችላል። “እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ (ሳዖልን) አገኙት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፥ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ” (1ሳሙኤል 10፡10)። ሳዖል በዚህ አልቀጠለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ወደኋላ በሳዖል ህይወት የሆነውን ሲናገር፤ “የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳዖል ራቀ፡ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሰቃየው” ይላል (1ሳሙኤል 16፡13)። ከዚህ ላይ እንደምረዳው በታላቅ ተስፋና ችሎታ ሥራውን ጀምሮ የነበረው ሳኦል በእግዚአብሔር ተተወ። መንፈስ ቅዱስ ሲተወውም የጭንቀት መንፈስ ያዘው፤ በቅናት፣ በንዴት፣ በቂምና በበቀል ተሞላ። ዳዊትንም ለመግደል ተደጋጋሚ ሙከራ አደረገ።

ዳዊት ይህንን በመንፈስ የመተው ውጤት በሳዖል ሕይወት ውስጥ አይቶታል። ስለዚህ እግዚአብሔር ለእንደዚህ ዓይነት ሕይወት አሳልፎ እንዳይሰጠው አጥብቆ ለመነ። “ጌታ ሆይ ይህ በሕይወቴ እንዲሆን አትፍቀድ!” በማለት የመጸለዩ ምክንያት ይኸው ይመስላል። ዳዊት የሳዖል ዕጣ ፈንታ እንዳይደርሰው ጸለየ። ይህ የዳዊት ጸሎት ያለ እግዚአብሔር መንፈስ ምሪት፤ ራሱን በራሱ ለመምራትም ሆነ አገሩን ለመምራት እንደማይሆንለት ከማስተዋል የመጣ ጸሎት ነው። መንገዱን አላውቀውምና ይህንን ሕዝብ በጥበብ መምራት አይሆንልኝምና መንፈስህን አትውሰድብኝ በማለት ተማጸነ።

ዛሬ የእግዚአብሔርን ጸጋ፣ በረከትና ምሪት ወደ ሕይወታችን የሚያመጣልን ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ያስፈልገናል። መንፈሱ ከተወሰደብን ሁላችን የጠፋን ነው የምንሆነው። ስለዚህ ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብን እንበለው። ያለ እርሱ መጸለይም፣ መዘመርም፣ ማምለክም፣ ማገልገልም፣ መኖርም አይሆንልንም። እርሱ ከእኛ ከተለየን ቃላችን እንደሚጮህ ጸናጽል ነው፤ እርሱ አስተማሪያችን፣ መሪያችን፣ ረዳታችንና አጽናኛችን ነው። ያለ እርሱ መኖር አንችልም (ዮሐንስ 15፡5)።

አንድ ወንጌል ሰባኪ በአንድ ወቅት እንደተናገረው፣ “አንዳንዴ እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ በድፍረት መጸለይ ያቅተኛል፤ አንዳንዴ ደግሞ እንደ ዳነ ክርስቲያን እንኳ መጸለይ ያቅተኛል፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የማመሰግነው፣ እንደ ኃጢያተኛ መጸለይ ግን ሁልጊዜ በመቻሌ ነው፤ ኃጢአተኛቴ ሲሰማኝ፤ አንገቴን ሲያስደፋኝ፣ ኅሊናዬ ክፉኛ ሲወቅሰኝ፤ “እኔን ኃጢአተኛ ይቅር በለኝ” በማለት ወደእርሱ እመለሳለሁ” ብሏል።

ሌላው ማስተዋል የሚገባን ነገር ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ከግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ከቤተክርስቲያንም የሚወስድበት ጊዜ ስላለ ይህ የማስጠንቀቂያ ደወል ለመላ ቤተክርስቲያን ጭምር እንዲያገለግል የተሰጠ ነው። ኃጢያት በቤተክርስቲያንም ሆነ በግል ሕይወታችን ነግሦ ሲገኝ መንፈስ ርቆን ሊሄድ ይችላል። ጌታ ራሱ በራዕይ መጽሐፍ እንደተናገረ መቅረዙን ከቤተክርስቲያን ሊያስወግድ ይችላል (ራዕይ 2፡5)። ስለዚህ በቤ/ክንም ሆነ በግል ሕይወታችን መራራ ሥር ሲኖር፣ ክፍፍል ሲኖር፣ የስህተት ትምህርት ሲኖርና ብዙዎችን ሲመርዝ፣ በአንድ ወቅት የእግዚአብሔር ክብር የተገለጠባት ቤ/ክን በቁጥር እየቀነሰችና እየኮሰሰች ጸጋ ሲሸሻት፣ የእግዚአብሔር ኃይል የማይገለጥባት ስትሆን፣ በቤ/ክንም ደረጃ ሆነ እኛ በግላችን በእግዚአብሔር ፊት በንስሐ ልንቀርብ ይገባናል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ የራቃት ቤ/ክ እጅግ በጥፋት መንገድ ውስጥ የምትገኝ ስለሆነ ነው።

የእግዚአብሔር መንፈስ ከግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብም፣ ከመንደርም፣ ከሀገርም ሆነ ከዓለም የሚለይበት ጊዜ አለ። የአምላክ መንፈስ ሲለየን ለእርስ በርስ ያለን ፍቅራችን ይቀዘቅዛል፤ ወንጀል በየቦታውና በየሀገሩ ይበረክታል። ጥላቻ በሕይወታችን ይነግሳል። በክፋታችን ያለመጸጸት እየቀጠልን እንሄዳለን። የእግዚአብሔር መንፈስ ይለየናል። የክፉ መናፍስት ማደሪያ እንሆናለን። ጌታችንና መድኃኒታችን እንደተናገረው “ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። በዚያን ጊዜም፦ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” (ማቴዎስ 12፡43-45)።

“በብርቱም ድምፅ፦ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች” (ራዕይ 18፡2)።

የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳምሶን ሲለይ፤ ለሳምሶን በጠላቶቹ መሸነፍ፣ ለዓይኑ መታወርና ለጽኑ እስራቱ ምክንያት ሆነ። ለሳዖል ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእርሱ ሲለየው ጥላቻ ነገሠበት፣ ተቅበዝባዥና ሥነልቦናው ያልተስተካከለ ሕይወት አገኘው። ሳዖልን የእግዚአብሔር መንፈስ ሲርቀው ተስፋ ቆረጠ፣ በመጨረሻም የራሱን ሕይወት አጠፋ። ስለዚህ እንደዚህ የከፋ ሕይወት ውስጥ ከመውደቃችን በፊት ወደ አምላክ በንስሐ እንመለስ፤ ከንጉሥ ዳዊት ጋር እንዲህ ብለን እንጸልይ፤ “አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ … አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ”።

ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ


የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

1 thought on “ቅዱስ መንፈስህን አትውሰድብኝ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *