የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሳምንቱን የሥራ ሰዓትን በተመለከተ ታላቅ ለውጥ ማድረጓ ተዘገበ። የሳምንቱ የዕረፍት ቀናት እሁድንም የሚያካትት እንዲሆን ተደርጓል። ውሳኔው እሁድን ዓለምአቀፋዊ የዕረፍት (ሰንበት) ቀን የማድረግ አንዱ ዕቅድ ነው ተብሏል።
በመንግሥት ይፋ በተደረገው መረጃ መሠረት የባሕረ ሠላጤዋ አገር ኤምሬትስ ዕረፍት ቀናት አርብ ግማሽ ቀን፣ ቅዳሜና እሁድ ሙሉ ቀን እንዲሆን ተወስኗል። ይህ ውሳኔ ከሌሎቹ ሙስሊም አገራት ለየት በማለት ኤምሬትስ የሥራ ቀናት 4 ቀን ተኩል (4.5)፤ የዕረፍት ቀናት ደግሞ ሁለት ቀናት ተኩል (2.5) እንዲሆኑ አድርጋለች።
ውሳኔው ሁለት ምክንያቶች እንዳሉት ነው የተነገረው፤ አንዱ ኤምሬትስን አጭር የሥራ ቀናት ያላት የአካባቢው ብቸኛ ሙስሊም አገር የሚደርጋት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱን እንደ ምዕራባውያን አገራት የቅዳሜና እሁድ ዕረፍት ቀናት የምትከተል ምዕራብ ዘመም አገር ያደርጋታል ተብሏል።
እስካሁን ድረስ በሙስሊም አገራት የተለመዱት የዕረፍት ቀናት አርብ (ጁማ) እና ቅዳሜ ነበሩ።
“ዘለግ ያለው የዕረፍት ቀን ማኅበራዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥና የሥራ-ዕረፍት ምጣኔን በማበልጸግ የኢኮኖሚ ተፎካካሪነታችንን ለማሳደግ መንግሥታችን እየወሰደ ካለው” እርምጃ አንዱ ነው በማለት መንግሥታዊው ሚዲያ ዘግቧል።
ለውጡ በመጪው የአውሮጳውያን ዓመት መጀመሪያ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን ከሰኞ እስከ ሐሙስ የሥራ ሰዓታት ከጠዋት 1፡30 እስከ ከሰዓት በኋላ 9፡30 ይሆንና አርብ ከጠዋት 7፡30 እስከ እኩለ ቀን (6፡00) ብቻ ይሆናል ተብሏል። ከአርብ ከሰዓት ጀምሮ ቅዳሜና እሁድ የዕረፍት ቀናት ይሆናሉ።
ውሳኔውን ዩኒቨርሲቲዎች፣ የግል ትምህርት ቤቶችና ድርጅቶች በሙሉ እንደሚያከብሩት ገልጸዋል። ከቅዳሜ እስከ ረቡዕ የሥራ ቀናት ይከተሉ የነበሩ ሁሉ በዚህ መንግሥታዊ ውሳኔ የሥራና የትምህርት ሰዓታቸውን እንደሚያስተካክሉ አስታውቀዋል።
መንግሥታዊው ሚዲያ እንደተናገረው ውሳኔው በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና ቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አጠቃላይ ተጽዕኖ በማጥናት የከናወነ መሆኑን በመግለጽ “ለዜጎችና ለነዋሪዎች የተሻለ፣ አስተማማኝና አስደሳች የኑሮ መንገድ እንደሚከፍት ይታመናል” ብሏል። በዚህም የቅዳሜና እሁድ ዕረፍት ቀናትን ከሚከተሉ ምዕራባዊ አገራት ጋር የተሻለና የጠበቀ ግንኙነት ለማድረግ እንደሚረዳ ተገልጾዋል። ይህም ኤምሬትስን ከዓለምአቀፉ የንግድ፣ የገበያ፣ የባንክ፣ የአክሲዮን ወዘተ ንግድ ጋር በማስተሳሰር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራት ያደርጋል በማለት አስታውቋል።
ጊዜው መጽሔት “ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ የመጀመሪያውን የአረብ ምድር ጉዞ ያደርጋሉ” በሚል ርዕስ የዛሬ ሦስት ዓመት ባወጣው መረጃ የሊቀጳጳሱ ጉብኝት በዓይነቱ የመጀመሪያና ታሪካዊ እንደሆነ ዘግቦ ነበር። በወቅቱም ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ እጅግ በርካታ ሕዝብ የተሰበሰበበት የመጀመሪያውን የአደባባይ ሥርዓተ ቅዳሤ (ማስ) ማድረጋቸው ይታወሳል።
ዓለምአቀፋዊ የወንጌል ሰባኪ የሆኑት ዳግ ባችለር የሊቀጳጳሱ የ2019 የኤምሬት ጉብኝት ጊዜውን ጠብቆ ይህንን ውሳኔ እንዳስገኘ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል። በመሆኑን 13በመቶ (800,000) የሚሆኑትን በኤምሬትስ የሚገኙትን ሠራተኞች የእሁድ ዕረፍት ቀን እንዲኖራቸው የሊቀጳጳሱ የዚያን ጊዜው ጉብኝት ፍሬ ነው ይላሉ። ይህም እስካሁን እሁድን እንደሥራ ቀን ይጠቀሙ የነበሩ የሙስሊም አገራት እንዴት እሁድን የዕረፍት ቀን አድርገው በመቀበል በዓለምአቀፉ የእሁድ ቀን አምልኮ እየተባበሩ እንደሚመጡ አንድ ማሳያ፤ ይህንን ለማያምኑ ደግሞ የማንቂያ ደወል ነው ብለዋል።
የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የሰንበት ቀን ከቅዳሜ ወደ እሁድ እንደቀየረች በይፋ ትናገራለች።
ለረጅም ዓመታት የቅዳሜ ሰንበትነት በአገራችን ይከበር የነበረ ሲሆን የምዕራባውያን በተለይም የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተጽዕኖ እየተስፋፋ ሲሄድ እሁድን እንደ ሰንበት ማክበር እንዲጀመር ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
በመካከለኛው ዘመን የአውሮጳ መንግሥታትን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ የነበረችው የሮም ቤ/ክ ኢትዮጵያ ይህንን የእሁድ ቅድስና እንድትከተል ምዕራባውያን መንግሥታት ጭምር በመጠቀም ፖለቲካዊ ግፊት አድርጋለች። አንቀበልም በማለት የተቃወሙና ሰንበት ቅዳሜ ነች በማለት በእምነታቸው የጸኑ እንደ ደቂቀ እስጢፋኖስ ያሉት እጅግ አስከፊና አሰቃቂ ስደትና መከራና ሞት እንደደረሰባቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ደቂቀ እስጢፋኖስ፤ በሕግ አምላክ” በሚለው መጽሐፋቸው በሥፋት ጽፈዋል።
ጊዜው መጽሔት